ትግሉን ሁለመና አንድ ሰው ላይ ማንጠልጠል አደጋው የከፋ ነው!

አርበኛ መሳፍንት የትግሉ አካል እንጂ የትግሉ ሁለመና አይደሉም! አርበኛ መሳፍንት የትግሉ አካል እንጂ ሁለንተናውም አይደሉም! አርበኛ መሳፍንት በትግሉ ውስጥ የራሳቸውን ታሪክ በደማቅ ሊፅፉ ነፍጥ ያነሱ ጀግና ናቸው! ሆኖም ግን ወደ ከተማ በድርድር ና ግባ ሲባሉ የቤት ባሪያው ብአዴን/አዴፓ ሸፍጥ አስቦ እንደሆን ልብ ይሏል! ብአዴንና ቀጣሪው ትግሉን አንድ ሰው ላይ ለማንጠልጠል እየተጣጣሩ ይገኛሉ:: አርበኛው ያ ባይሆንም አላማቸውና ፍላጎታቸው! ለምን ብአዴን ይህንን ሸፍጥ ፈለገው ስንል መልሱ ትግሉ አንድ ሰው ላይ ተንጠልጥሎ ሲያበቃ አርበኞችን በስውር ሴራ በማስገደልና በማሳፈን የብሄርተኝነቱን ቅስሙን ለመስበር ታስቦ ነው! በሌላ ጎን ደግሞ ብአዴን እድሜውን ማስረዘሚያ ዘዬ በሸፍጥ ሁሉን በልጦና ጎልብቶ ሁሉን ውጦ ከፍ እንዳለ ለማስመሰል ለኃላው እያሰበ ነው! መላው አማራ መጠንቀቅና አስተውሎ በጠላቶቹ ልክ ማሰብና መራመድ ካልቻለ ከፊቱ ትልቅ አደጋ ይጠብቀዋል!

አማራ ብሄርተኝነት/ትግል በአንድ ድርጅት ላይ ብሎም በአንድ ግለሰብ ላይ ሁለንተናውን ማስለካት ልንወጣው ወደማንችበት አዘቅት ይከተናልና ቆም ብለን እያሰብን ከስሜት በፀዳ  አህምሮን ባማከለ  እጅግ በረቀቀ ስልት  በጥበብና ማስተዋል ሁሉን እናደርግ ዘንድ ጠላቶቻችን በዚህ መልክ ሰልተዋል!

ፍከራ እና ማቅራራት በእርግጥ የጀግና ነው ሆኖም ጀግና ተሰጋጅቶ ሁሉን በውስጥ ጨርሶ ይፎክር ዘንድ ባህሉ ያ ነው:: ብአዴን የጀርባ አጥንት የለውምና ያገኘው ዛፍ ይሁን እንጨት ላይ መንጠላጠል ይወዳል! ተጎትቶ ያገኘው ዛፍ ላይ ተጠምጥሞ እንደ እባብ መርዙን ለማሳት የሚተፋ እኩይ ነው! ከምድር ብሄር ድርጅቶች ሁሉ ተለይቶ የተረገመ ነውና አፈር እየላሰ እየተነሳ መሬት ላይ እየተሳበ የአማራን ትግል መንደፉን ተያይዞታል::

አርበኛ መሳፍንትን የትግሉ ሙሉ ቁመና ማሸከምና በእሳቸው ዙሪያ ብቻ ለማጠር ብአዴን መድረኮችን በማመቻቸት አርበኛውን ከስፍራ ስፍራ እያዘዋወሩ ያደክሟቸው ይዘዋል:: የአርበኞች አላማ አንድ ነው- ነፃነት! ብአዴን ግን የተለያየ እጅ መንሻ እያቀረበ ነው:: አርበኞች እስከአሁን ንቀው እቢኝ ብለው እንጂ አርበኛውን ሁሉ እርሻ መሬት ሰጥቶ ለራሱ ሆድ ሲል ወደ ቀለብ አዘጋጅነት ሊያስገባ ይታትራል:: ብአዴን ዋና ጠላታችን ነው ስንል በምክኒያት ነው! ጉበኞች!

አርበኞች ለምን ከተማ መጡ?

አርበኞችን አባብሎ ወደ ሰፈር ማስገባት ለምን አስፈለገ? እኛ ገና የምንጋጠመው እንጂ ድል ያደረግንበት ጦር ሜዳ የለም ገና! ጭልጋ ላይ እኮ እየተደበደብን ነው ያለነው! ማነው ይህንን ትርኢት sponsor አድራጊው? ለምን? ልንጠይቅ ይገባናል የህልውናችን ጉዳይ ነውና! ወገን አደጋ ላይ ነን! ብአዴን አሳልፎ ሰጥቶ “መሻሻል አለብን ችግር አለብን” የሚል የባሪያ መልስ ሰጥቶ ተከናንቦ ይተኛል እኛ ግን ትልቅ ጉድለት ይሆንብናል! በወደረኞቻችንም ፊት ያኮሰምነናል! ከሁሉም ባለፈ ገና በደንብ ድክ ድክ የማይለው ብሄርተኛ ሞራል ይወድቃል ነገ እነኝህ አርበኞች ጥቃት ቢደርስባቸው በከተማ ሳሉ ስብራታችን የከፋ ነው የሚሆነው!

ትግሮች ድምፅ አጥፍተው እየሰሩ ነው! ድምፅ አጥፍተው እየተዘጋጁ ነው! በለሆሳስ ስልት እየቀየሱ ነው:: የተሸነፉ መስለው  አቅመ ቢስ መስለው ድር እያደሩብን እያደቡብን ነው! ከጠላት መማር ትልቅ ብልጠት ነው! ድምፅ አጥፍተን  ፉከራዉን ለነገ አድርገን በዝምታ ውስጥ ለውስጥ መታጠቅ  መደራጀት  ስልት መንደፍ ይጠበቅብናል! እኛ ብቻ ነን የምፎክረው ያለነው! ብቻችንን ነው ቀረርቶውን የተያያዝነው:: ጠላት ግን ለምሽግ ጉድጓድ እየቆፈረ ነው! ጠላቶች ግን ለአደጋ ግዜ የሚያስፈልግ መሳሪያ እህልና ቁስ እያከማቹ ነው:: እኛ ደግሞ በከተማ ውስጥ ፍከራ ላይ ብቻ ሰማይን ልንበሳ ይመስል ጥይት እናንጣጣለን! ወደ ላይ የሚተኮስ የለንም ወደ ጎን እንጂ!

ጠቢብ ድምፅ አጥፍቶ ነው የሚሰራው! እዚህም ሰፈር የጥይት ተኩስና ፍከራውና የትግል ሰለብሪቲ ፎቶ ጦፏል:: የብአዴን ግሪሳ በሚሰጠው ላይክና ሼር ሰለብሪቲ የሆኑ የሚመስላቸው ሞኝ አክትቪስቶች አሉ:: የፃፍከው ብአዴንን አጀንዳ እስካልነካ ላይኩ እንዲሰጥህ ታዟል! እናም ላይክህ ጣራ ሲነካ የፃፍከው ነገር እድር ቤታዊ ስለሆነ ነው:: ቆንጠጥ አድርገህ ያለውን እውነታ ስታፈርጥና ፖለቲካውን በሳይንስ ስትፈታ ላይክህ ተሽቆልቁላ ወደ ድሮው ቦታዋ ትመለሳለች! Popular thought እያስኮመኮምክ ግሪሳው የፌስቡክ ብአዴን ስራዊት ጣራ ሲያስነካልህ ውሀ የሚያነሳ ነገር የፃፍክ እንዳይመስልህ! ይልቅ የልብ የልቡን እናውጋ! አንጠላለፍም የሚል የእረኞች ጨዋታ አይነት ጫጉላ ሽርሽር ፖለቲካ አይደለም ካድሬነት እንጂ! በእርግጥ አንዳንዶች ካድሬ መሆናቸውን እንኳ አያውቁትም ግን ናቸው! የማይከፈላቸው የላይክ ናዋዥ ካድሬዎች

በአንድ ቅርጫት እንቁላሉን ሁሉ ማስቀመጥ አደጋ አለው!

በመቀጠል አማራ በየስፍራው 15-35 ሰው እየሆነ መደራጀት ይኖርብታል:: አማራ በአንድ ድርጅት ጥላ ስር ለመሰባሰብና በአንድ አካል ተጠሪ ለማግኘት መሞከር አሁን ባለበት የትግል ደረጃ ሌላኛው ዋና አደጋ ነው! አንድ ቅርጫት ውስጥ እንቁላሎች ሁሉ ከተገኘን እዛው መታሸት ይሆናል::ፕራክቲካልም አይደልም! የሚቻልም አይደለም! ለምን? አንድ ድርጅት ብቻ ከወከለን የድርጅቱ ውስጥ ሚስጥርን የሚያባክኑ ሰዎች በማስረግ ዱካ ተከትሎ አጥፊው ማይፋት ይችላል:: በየስፍራው ግን ፈነዳድተን በዝተን ለመያዝ ለመጨበጥ አዳግተን ወረርሽኝ መሆን ይጠበቅብናል! በአሁኑ ሰአት አማራው ብሄርተኝነት ገና የለም ማለት ይቻላል ካለን ብዛት አንፃርና በተለይም በጥራቱ ስንለካው! አስታውሳለሁ ብዙ ልጆች ያፈራን መስሎን ጥቂት የማይባሉ “እቢ አላነሳም እጄን ከቀሚሷ” የሚል የሞኝ ዘፈን ሰምተው የኮበለሉና አማርነት ላሳር ብለው ወደ ኢቶጴነት ወደው የገቡ ነበሩ:: ብዙ ዥዋዥዌ የሚበዛበት ነው የኛ ትግል: ገና ብሄርተኝነት ማለት ምን ማለት ነው የሚለውን በስነ ስርአት ያሰረፀ ድርጅትም ሆነ ግለሰብ የለም! ዝም ብሎ በደፈናው አማራ አማራ እያለ የሚጮኽ ነው የሚበዛው:: ያ ብሄርተኝነት ነው ልንለው አንችልም! የብሄርተኝነት እንደ አፍ መፍቻ ያለ ቋንቋ የምንተባተብበት የአራስነት “ታ ታ ማማ” የምንለው ቋንቋ አይነት ነገር ነው:: አብዛኛው ከእንቅልፉ ሲነሳ አማራ ማታ ሲተኛ ኢቶጴ ነው:: ብሄርተኝነት የራሱ ሳይንስ አለው: ብሄርተኝነት አንድን ማህበረሰብ ገርቶ በአንድ መናበብ ማሰለፍ የሚያስችል ትልቅና ከባድ ሳይንስ ነው: እዛ ላይ እየተሰራ አይደለም ብል ውሸት አይሆንም! በብዙ ፅሁፎችና ኢንተርቪዎች የምሰማቸው እንኳ እዚህ ፌስቡክ ላይ ትግል ስንጀምር ለፕሮቮኬሽን የተጠቀምናቸውን አባባሎችና ሌሎችም በትግሉ መጀመሪያው ደረጃ ላይ የፃፋቸውን ያልናቸው ነገሮች ነው ተደግሞ ተደጋግሞ ከየአቅጣጫው የምሰማው! ይኸ ደግሞ የሚያሳየን የራሱን ፕሮግራም የፃፈም ሆነ የማስረፅን ስራ የሚሰራ እንደሌለ ነው:: ይታያችሁ ዛሬ እኮ ጎንደር ላይ የግምቦት ዜሮ ባነር ተለጥፏል! ደብረማርቆስ የግም ዜሮ የፖለቲካ ኪዎስክ ተከፍቷል! ደብረታቦር ላይ እኮ ግም ዜሮ ይፋንናል ያለው! የቱጋር ነው የኛ ብሄርተኝነት ያለው ታዲያ? ” ቃሉን የሚሰብኩ ከሌሉ እንዴት ይድናሉ” እንዲል ቃሉ ያላሰረፅነው ብሄርተኝነት እንደ ሙጃ በራሱ አይበቅልም! ካልተኮተኮተ ውሀ አይገባም ጠብም አይልበትም! ጓጓላውን ካልከሰከስነው ጅብራ ይሆናል አንድ ቀን መንገድ ሊዘጋ ይችላል! ብሄርተኝነት የታታሪ ገበሬ አይነት ስራን ይሻል! ሞፈሩን ከጅራፉ ይዞ በአንድ እጁ እየሾጠም በሌላ እጁም ማረሻውን እየገፋ ነው ብሄርተኛ እናም ዛሬ ባንድ እጄ ልሾጥ በጅራፍ በሌላኛው ላርስ ይህን ፃፍኩኝ!

የህልውናችን ትግል ሁለመናው በሁላችን ትከሻ ላይ ይረፍ! ግዳጁን እያንዳንዱ አማራ ይወጣ!

በአመክንዮ ሞግቱ ስድብ አቁሙ!

ሊዲያ ዘ ጊዮን አማራ