Home ታሪክ በረራ አዲስ አበባ/እንጦጦ ናት!

በረራ አዲስ አበባ/እንጦጦ ናት!

2

በረራ አዲስ አበባ/እንጦጦ ናት!

ማህበራዊ ሚድያ ላይ ያለውን ሞቅታ ተከትሎ በፈረንጆች መስከረም 30 ቀን 2018 ሳሙኤል ዎከር የተሰኙ ጸሐፊ አዲስ ፎርቹን ላይ “እንጦጦ በረራ አይደለችም” የሚል ጽሑፍ አስፍረው ነበር። አቶ ዎከር አሁን አዲስ አበባ የምትገኝበት አካባቢ (እንጦጦን ጨምሮ) የመካከለኛው ዘመን በረራ ትገኝበት የነበረው ነው የሚለውን ምሁራዊ ድምዳሜ “መሰረተ ቢስ”፤ “ጥራዝ ነጠቅ” እና አደገኛ ቂልነት ሲሉ አጣጥለውታል።

ስለዚህ ጉዳይ የምለው ይኖረኛል። የአሁኗ አዲስ አበባ በረራ መሆኗን የሚገልጽ ጣቃ  ሙሉ ማስረጃዎች አሉ። ቀጥሎ ከምንዳስሳቸው ማስረጃዎች በተጨማሪ ወጨጫ/እንጦጦ ከ1530ዎቹ የኢማም አህመድ ኢብራሂም ወረራ በፊት የነበረችው የመካከለኛው ዘመን በረራ መሆኗን አፈታሪኮች ሳይቀር ይናገራሉ። የዚህ ጽሑፍ ዓላማ እንጦጦ በረራ አይደለችም የሚለውን ለመሞገት አይደለም። የአቶ ዎከርን አድሎዊ ደብዳቤ ፖለቲካው አንድምታ ለመሻርም አይደለም። ከዚህ የባሰውን የዎከርና መሰሎች በኢትዮጵያ አልፎ ተርፎም በአፍሪካ ታሪክ ላይ የሚያራምዱትን ግድየለሽነት የተሞላ የማንሸዋረር ሂደት ማጋለጥ ነው።

  አቶ ዎከር 24 ዓመታትን በቆየበት የሥራ መስኩ በዓለማቀፍ የምርምር ጥራዞች ላይ አንድም የታተመ የምርምር ሥራ ሳይኖረው በመስኩ ራሱን እንደጠቢብ ማየቱና የሌሎችን የምርምር ሥራዎች ማጣጣል እንደሚችል ማሰቡ የሚገርም ነው። የዘለቀው እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ሲሆን ሦስተኛ ዲግሪውን እንኳን ለመያዝ አልሞከረም። ዎከር ለኔ መካነ አዕምሮ ጎብኝ (Academic tourist) አካል እንጂ ቁም ነገር ያለው ባለሙያም አይደለም። የዎከር ሊንክዲን ማህደር ኮንጎ ተወልዶ ኬንያ እንዳደገ፤ በአሜሪካና በብሪታንያ ታሪክ፤ ንፅፅረ-ሃይማኖት፤ የመሬት ሳይንስ፤ ሥነ አጽም፤ የውርስ ጥናት እና መሰል መስኮችን እንዳጠና ያትታል። ዎከር ለ15 ዓመታት በየመን፤ እስራኤል፤ ዌስት ባንክ እና ዮርዳኖስ አስተማሪ፣ የስነ አጽም ባልሞያ እና ተመራማሪ ሆኖ በተመሳሳይ ጊዜ እንደሰራ ይገልጻል። ዎከር ለ7 ዓመታትም ማይክሮኔዥያ (ምዕራባዊ ሰላማዊ ውቅያኖስ) እንደ ስነ አጽም ባለሞያ እና የአካባቢ ሳይንስና የአየር ንብረት ለውጥ አስተማሪ ሆኖ እንደሰራ ጽፏል። ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ አዲስ ግኝቱ በሆነችው ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ኑሮውንና መስሪያ ቤቱን አድርጓል።

  ዎከር ኢትዮጵያ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ (6 ዓመታት እንኳን አልሞሉትም) አያሌ መስሪያ ቤቶችን ቀያይሯል። ከሌሎች በተጨማሪ ዎከር አዲስ አበባ የሚገኘው የሴንት ሜሪ ኮሌጅ አስተማሪ ሆኖ የሰራበትና የቅርስና ውርስ ዋና አማካሪ ሆኖ ያገለገለበት የሚጠቁሱ ናቸው። ዎከር ጥብቅ ቁርኝት ካለው አክሱም ዩኒቨርሲቲ ጋር ሆኖ የስነአጽምና ውርስ አስተዳደር የሁለተኛ ዲግሪ መርሃግብር ለመጀመር እዚሁ ዩኒቨርሲቲ ጋር እንቅስቃሴ ላይ ነው። አሁን ደግሞ የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ ነኝ ብሎ መጥቷል። ወረቀት ላይ ሲታዩ ከ20 ዓመታት በላይ ሰራሁባቸው ያላቸው መስኮችና የስራ ልምዱ አማላይ ይመስላሉ። ነገር ግን ካገር አገር መዟዟሩና ብዙ አይነት የትምህርት አይነቶችን መነካካቱ ከምንም አይነት የታተሙ የምርምር ውጤቶች አለመኖር ጋር ተደምሮ ሰውየው ባንዱም የጠለቀ ግንዛቤ እንደሌለው የሚያይ ነው።

 ዎከር ስለ በረራ የጻፈውን ደብዳቤ ካነበብኩና አርፎ አይቀመጤ የሊንክዲን ማህደሩን ካየሁ በኋላ በዶ/ር ፖል ትያምቤ ዘሌዛ ሥራ ላይ የተጠቀሰው ሀሳዊ ፕሮፌሰር ፕሮፌሰር ክሌግን ትዝ አስባለኝ። ፕ/ር ክሌግ ባንድ ቦታ ረግቶ የማይቀመጥ አትራፊ የመሰለውን የጉዞ ጋሪ ዘሎ የሚሳፈር ዋሾ የትምህርት ተቋማት ጎብኝ (academic tourist) ሰው ነበር። አብዛኛው ጥልቀት የሚጎለውን  አፍሪካዊ ተመራማሪ  በክሌግ ይመሰላል እና ነው።

ወደ ዎከር ቀልባችን እንመልስና፤ አፍሪካን፣ መካከለኛው ምስራቅን እና ማይክሮኔዥያን ያካለለውና ከአገር አገር የሚያዘልለው አቅሉ የመካነ አዕምሮ ጎብኝ የሚያስብል እንጂ ባለ ልምድ ሞያተኝነትን አይገልጽም። የስራ ማህደሩ በብዙ ዘርፎች “የተካነ” እና ሶስት ክፍለ ዓለማትን ያማተረ መሆኑን ያሳያል። ነገር ግን ስለአንድ አገርም ሆነ ባንድ የሙያ ዘርፍ ለመካን የዕድሜ ልክ ጽናትን ይጠይቃል። አቶ ዎከር ግን ልክ እንደ ፕ/ር ክሌግ በዘፈቀደ ሞያውንና መስሪያ ቤቱን እየቀያየረ በየገባበት ሁሉ “የተካንሁ ነኝ” ይላል። ይህን ሁሉ ለማንሳት የተገደድነው ያለሞያው ገብቶ ስለመካከለኛው ዘመን በረራ ያሰፈራቸው ተንኳሽና መረተቢስ ድምዳሜዎች የተነሳ ነው።

 ዎከር ልክ እንደ ፕ/ር ክሌግ የትኩረት ማነስ ይታይበታል። ዎከር በራሱ አንደበት እንጦጦን እንደጎበኘ እንጂ ምንም አይነት የስነ አጽም ምርምር በቦታው እንዳልሰራ ተናግሯል። ይህም ብቻ ሳይሆን በቦታው የስነ አጽም ምርምር የሰሩ ሰዎችንም በማጣቀሻነትም አልገለጸም። ስለዚህ “እንጦጦ በረራ አይደለችም” የሚለው ደብዳቤው ያለምንም ታሪካዊ እና ስነ አጽማዊ ማረጋገጫ ነው። የደብዳቤውን ሙሉ ሀሳብ ሙሉ በሙሉ ለማንሳት ቦታ ባይበቃኝም የተወሰነ አንኳር ነጥቦችን ግን ወደ አንባቢው ትኩረት ለማምጣት እወዳለሁ።

 

አንደኛ፤

ዎከር እንጦጦ ላይ የሚገኙ ቅሪት አካላት ዕድሜ ከበረራ ውድመት በአንድ ክፍለዘመን ያነሰ ነው ይላል። ይህ የኢትዮጵያ ታሪክን ቅደም ተከተል ችላ ያለ ነገር ነው። የኢማም አህመድ ኢብራሂም ዘመቻዎች ዜና መዋዕል ጸሐፊ አረብ ፈቂህ በረራ የወደመችው በ1530 ነው ይላል። በዚህ ሁላችንም እንስማማለን። ነገር ግን ዎከር እንጦጦ ላይ የተገኙት ቅሪት አካላት የተገነቡት በ1630ዎቹ ነው ይላል። ከ1580ዎቹ ጀምሮ እንጦጦ አካባቢ ከኢትዮጵያ ቁጥጥር ውጭ ሆኖ ስለነበር ቅሪት አካሎች “በ1630ዎቹ የተሰሩ ናቸው” የሚለው የዎከር ድምዳሜ የጊዜ ቀመርን የሚያፋልስ ነው። በተጨማሪም በረራ በ1531 ከወደመች በኋላ ምንም አይነት ንጉሳዊ ሸንጎ እንጦጦ አካባቢ እንዳልነበር የሚታወቅ ነው። ከግራኝ ዘመቻ በኋላ የነበሩ የኢትዮጵያ ነገስታት አጼ ገላውዴዎስ (እስከ 1559)፤ አጼ ሚናስ (እስከ 1563)፤ አጼ ሰርፀ ድንግል (እስከ 1597)፤ አጼ ሱስንዮስ (እስከ1632) ሁሉም በሚባል ሁኔታ ንጉሳዊ ዙፋናቸው ሌላ ቦታ ነበር። ባጭሩ፤ ከ1531 በኋላ ምንም አይነት ንጉሳዊ ዘውድ በቦታው ሳይኖር እንጦጦ አካባቢ የተገኙት ቅሪት አካል ከዚያ በኋላ (በ17ኛ ክ/ዘ) የተሰሩ ናቸው ማለት የጊዜ ንጉደትን የሚያፋልስ ነው።

 

 ሁለተኛ፤

የንግድ ማዕከል እንደነበረች የሚነገርላት በረራ “እንጦጦ ላይ ልትሆን አትችልም፤ ምክንያቱም የእንጦጦ መልክዓ ምድር ለነጋዴዎች ምቹ  ስላይደለ” ሲል ዎከር ይሞግታል። ይህ ሰውየው ስለ ኢትዮጵያ መልክዓ ምድር ያለውን ድንቁርና ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው። አቀበታማነት ተራሮች ጫፍ ላይ የንግድ ማዕከላትንና ከተሞችን ለመቆርቆር ችግር ፈጥሮ እንደማያውቅ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሊነግርህ ይችላል። አብዛኛቹ የኢትዮጵያ ከተሞች (በተለይ የጥንቶቹ) የተቆረቆሩት ተራራማ ቦታዎች ላይ ነው። ደማማቆቹ አምባ አላዩ፤ አንኮበር፣ ጎንደር፤የረር፤ ዋስል (ያሁኗ ደሴ) እንደምሳሌ ሊጠቀሱ ይችላሉ። እንዴውም ደጋማው የኢትዮጵያ ህዝብና ንጉሦቻቸው ከተራራማ ቦታዎች ጋር የጠበቀ ቁርኝት አላቸው። ረባዳማነትን ከንግድ ማዕከልነት ያያዘው ዎከር የአውሮፓውያኑ ባህል ስለተጣባበት ብቻ ነው።

ሦስተኛ፤

   ዎከር እንጦጦና የመካከለኛው ዘመን በረራ ምንም አይነት ባህላዊ ቁርኝት የላቸውም ይላል። ይህ ስለአካባቢው የተጻፉ መሰረታዊ የታሪክ ጽሑፎችን ካለማወቅ የመነጨ ነው። በ19ኛ መቶ ክፍለ ዘመን በሸዋ ያለፉ አውሮጳውያን የሃይማኖት ልዑካን፤ እንደራሴዎች፤ የጦር አበጋዞች፤ ነጋዴዎችና ጎብኝዎች ሁሉም በሚባል ሁኔታ አዲስ አበባ እና አካባቢው የኢትዮጵያ መካከለኛው ዘመን የመንግስት መቀመጫ እንደነበር ጽፈዋል። ከነዚህ ውስጥ ዮሐን ክራፍ አንዱ ናቸው። ዮሐን ክራፍ በ1840ዎቹ ሸዋን በደንብ የዞረ ጀርመናዊ የሀይማኖት ልዑክ ነበር። ክራፍ አዲስ አበባ የልብነ ድንግል (እስከ 1540) እና የሌሎች የመካከለኛው ዘመን ሰሎሞናዊ ነገስታት መቀመጫ እንደነበረች አስረግጦ ተናግሯል። ፈረሳዊው ተጓዥና እንደራሴ ቴዎፊል ሊፈቭረ የሸዋው ንጉስ ሳህለስላሴ (እስከ 1847) ወደ በአዲስ አበባና አካባቢዋ የተማረከው ከመካከለኛው ዘመን ጋር ካላት ቁርኝት እንደሆነ ጽፏል። ሌሎች በርካታ አውሮጳውያን ተጓዦችም የቤተ ክህነትና የቤተ መንግስት ቅሪት አካላትን አዲስ አበባ አካባቢ (እንጦጦን ጨምሮ) እንዳዩ በተደጋጋሚ ገልጸዋል። ሊፈቭሬ ከፍልውሃ በፈረስ አስር ደቂቃ ርቀት ላይ የመካከለኛው ዘመን የቤተ ክህነት ቅሪት አካል እንዳገኘ በስፋት ጽፏል።

 ሌላኛው ማጣቀሻ የዳግማዊ አጼ ምኒልክ መዋዕል ጸሐፊ የሆኑት ጸሐፊ ትዕዛዝ ገብረስላሴ የጻፉት ነው። ምኒልክም ሆኑ አያታቸው ንጉስ ሳህለስላሴ በሸዋ ንጉስነታቸው ወቅት የአጼ ዳዊት (እስከ እስከ 1412) ከተማን አጥብቀው ያፈላልጉ እንደነበር ጽፏል። እንጦጦ ላይ ቅሪት አካላቱን ሲያገኙ የአጼ ዳዊት ከተማ በዚያ መሆኑን ስለተረዱ መቀመጫቸው በዚያ እንዲሆን ወሰኑ። የፈረንሳይ ተመራማሪዎችም የእንጦጦ ራጉዔል ቤተ ክርስቲያንንና የሸዋ ሥርዎ መንግስት ታሪካዊ ቁርኝት በስፋት አጥንተውታል። ለመደምደም ያክል እንጦጦን ከአጼ ዳዊቷ በረራ ጋር የሚያዛምድ በርካታ ቅሪት አካላዊና ባህላዊ ቁርኝት እንጦጦ ውስጥ አለ። እንጦጦን ከመካከለኛው ዘመን በረራ ጋር የሚያቆራኝ ወግ የለም ያለው ዎከር ከተጠቀሱ ታሪካዊ መጻጽፎች ጋር ስላልተገናኘ ነው።

 

 አራተኛ፤

እንጦጦ አካባቢ ያሉ ቅሪት አካላት የግንባታ ትብያና የሸክላ ተረፈ ምርቶችን አያሳዩም የሚለው የዎከር ድምዳሜ ያለምንም የስነ አጽም ቁፋሮ የተደረገ ድምዳሜ ነው። የሸክላ ስራ ውጤቶች በቁፋሮ ብቻ ሊገኙ የሚችሉ መሆኑ እየታወቀ አካባቢውን በዐይን በማማተር ብቻ እዚህ ድምዳሜ መድረሱ የሚገርም ነው። የስነ አጽማዊ ቁፋሮ ካካሄደ በኋላ እዚህ ድምዳሜ ላይ ቢደርስ ኖሮ ምልከታው ተቀባይነት ይኖረው ነበር። ላሊበላን የሰሩ አባቶቻችን ለምሳሌ ህንጻዎቹን ካነጹ በኋላ ለህንጻ ግንባታ የተጠቀሙባቸውን ቁሳቁሶች አጽድተዋቸዋል። ለህንጻ ስራ የዋሉ ተረፈ ምርቶች ላሊበላ አካባቢ አይታዩም ማለት ቦታው በመካከለኛው ዘመን ሰው ሰፍሮበት አልነበረም ማለት አይደለም። በተመሳሳይ እንጦጦ አካባቢ የሸክላ ስራ ቅሪቶች አይታዩም ማለት በመካከለኛው ዘመን አካባቢው ሰው አይኖርም ነበር ማለት አይደለም። በመካከለኛው ዘመን ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ይጠቀሙበት የነበሩ ቁሳቁሶችን ለማወቅ ጥረት በማድረግ ፈንታ አቶ ዎከር የራሱን የይሆናል ሀሳብ መውሰድን መርጧል። የተገኙት የሸክላ ውጤቶች ዕድሜያቸው በረራ ጠፋችበት ከተባለው ዕድሜ በመቶ ዓመት ያነሰ ነው የሚለው ድምዳሜው ከላይ እንደተጠቀሰው አሁንም የጊዜ ቀመርን ያፋለሰ ሆኖ አግኝቸዋለሁ።

 

አምስተኛ፤

ዎከር “እንጦጦ አካባቢ የተገኙ ቅሪት አካላት አገር በቀል የኢትዮጵያውያን የስነ ህንጻ ባህልን አያንጸባርቁም፤ ስለሆነም እዚህ ግባ የሚባሉ ውርሶች አይደሉም” ያለበት ሃላፊነት የጎደለው ድምዳሜም ይገኛል። ይህ በውነቱ ቅሪቶቹን አፍርሰን ለዘመናዊ ህንጻ ግንባታ ግብአትነት እንድናውል የሚጋብዝ ነው። እንጦጦ አካባቢ የተገኙ ቅርቶች ጥበቃና እንክብካቤ እንዲደረግላቸው በማሳሰብ ፋንታ “ባዕድ እና የማይጠቅሙ” የሚልና እንዲወድሙ የሚያበረታታ ድምዳሜ ላይ ደርሷል። “ጠቃሚ ቅርስ” የሚለውን የሚወስነው ማነው? ዎከር የመካነ አዕምሮ ጎብኝው? ወይስ የቅርስ ጥናት መምሪያና የአካባቢው ነዋሪ? ሀቁ ግን የእንጦጦ ቅሪቶች አገር በቀል ባህልን የሚያንጸባርቁ አማላይ ቅርሶች ናቸው! የእንጦጦ የድንጋይ ግንብና ምሽግ (ባንድ ወቅት የድንጋይ ማማ የነበረ) ከጠንካራ አለት ተፈልፍለው የተሰሩ ናቸው። በ19ኛው መቶ ክፍለዘመን ወደ ኢትዮጵያ ከዘለቁ አያሌ ተጓዦች አንዱ የሆነው ኤድዋርድ ግሌይከን እንጦጦ ላይ ያየውን የድንጋይ ግንብና ምሽግ የሚገልጽበት ቃል አጥቶ እንደነበር ጽፏል። ድንጋይ ጠርቦ ሀውልት ማቆም፤ ቤተ መቅደስ እና ህንጻ ማነጽ የኢትዮጵያውያን የቆየ ልምድ ነው። እንጦጦ ራጉዔል ቤተክርስቲያን ጥግ ከድንጋይ ተፈልፍሎ የተሰራ ቤተ ክርስቲያን መሳይ ነገር አለ። አዳዲ ማርያም እና የካ (ዋሻ) ሚካዔል እንዳሉ ሆኖ። የእንጦጦ ቅሪት አካል ከየካ ሚካዔልና ከአዳዲ ማርያም ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ተነጥሎ የሚታይ አይደለም። ድንጋይ ጠርቦ ህንጻን የማነጽ ታሪክ ያላት አገር ውስጥ የእንጦጦ ቅሪት አካላት አገር በቀል አይደሉም ማለት ታላቅ ድፍረት ነው።

 

 ስድስተኛ፤

ዎከር “አዲስ አበባና አካባቢው ረግረጋማ ስለሆነ በረራ አዲስ አበባ ላይ ልትሆን አትችልም” ብሏል። እየሩሳሌምና ጣልያን ውስጥ በ15ኛው ክ/ዘ መጨረሻ ላይ የኖሩት የበረራ ተወላጅ አባ ቶማስ በረራ ወረብ የሚባል አውራጃ ውስጥ እንደነበረች ጽፈዋል። ወረብ አዲስ አበባንና አካባቢውን የሚያጠቃልል አውራጃ ነበር። በረራ በዘመቻ ከመውደሟ በፊትና በኋላ የሚያውቃት አረብ ፈቂህ በረራ ወረብ ውስጥ መሆኗል ገልጿል። አባ ቶማስም ሆነ አረብ ፈቂህ ወረብ ሰው በብዛት የሚኖርባት አውራጃ እንደነበረች እንጅ ረግረጋማ እንደነበረች አልገለጹም። አረብ ፈቂህ ብዙ ረግረጋማ ቦታዎችን ጠቅሷል፤ ወረብ ከነዚህ መካከል አንዷ አይደለችም።

 

ሰባተኛ፤

ዎከር “አዲስ አበባ አካባቢ ያለው መስክ የመካከለኛው ዘመን በረራን ነዋሪዎች ሊያጠግብ አይችልም” ያለው ተራ መላ ምት ነው። ከዎከር በተቃራኒ የመካከለኛው ዘመን ወረብ አውራጃ እጅግ ሲበዛ ለምና ምርታማ እንደነበር ነው የሚነገርለት። አረብ ፈቂህ ካንድ አይሉ ሁለቴ ወረብን “የአቢሲኒያ ገነት” ሲል ገልጿታል። ወረብ በቤተ ክህነት፤ ገዳማት ያሸበረቀች በዘመኑ ከነበሩ አውራጃዎች ውስጥ ሀብታሟ እና በጥራጥሬ ምርት የምትታወቅ ነበረች። ባጭሩ፣ አዲስ አበባ ዙሪያ የነበረው የእርሻ መሬት ወረብን “የመካከለኛው ዘመን ኢትዮጵያ የዳቦ ቅርጫት” ያሰኛት የአውራጃዋ አንድ አካል ነበር። እንደበረራ አይነት ታላቅ ከተማ ለማጥገብም ከበቂ በላይ ነበር። ዎከር ግን “አዲስ አበባ በመካከለኛው ዘመን ረግረጋማ ነበረች” ላለው እንኳን ማስረጃ ለማቅረብ አልሞከረም!

 

 ተፃፈ በዶክተር ሀብታሙ ተገኝ

ተተረጎመ በGM መላኩ